ግንቦት 22/2017 (ወልቂጤ)
******
የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመልካም ስነ-ምግባርና በክህሎት የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት እያደረገው ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የኮሌጁ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ላጫ ገሩማ ገለፁ።
ዋና አስተዳዳሪው ይህንን የገለጹት የኮሌጁ የቦርድ አባላት በተገኙበት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ያደርገ ግምገማ ነክ ውይይት በጉራጌ ዞን አገና ከተማ አስተዳደር በተካሄደበት ወቅት ነው።
የውይይት መድረኩን የመሩት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የኮሌጁ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ላጫ ጋሩማ የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመልካም ስነ-ምግባርና በክህሎት የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች በመሆኑ ይህንን ስኬት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኮሌጆች ከመንግስት የሚለቀቅላቸውን በጀትና ድጋፍ ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ በውስጣቸው ያሉትን ጸጋዎች በአግባቡ በመለየትና ሀብት በመፍጠር እራሳቸውን ከማስተዳደር አልፈው ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መሆን እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ላጫ የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም በዚህ ዘርፍ የተጠናከረ ስራ መስራት አለበት ነው ያሉት።
የጉራጌ ዞን ቴክኒክና ሙያ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ስርጋማ በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ትምህርትና ሥልጠናን ተደራሽነት በማስፋትና ጥራቱን የጠበቀ ስልጠና በመስጠት የስራ እድል ለመፍጠር እንዲችሉ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ለዘርፉ ውጤታማነት የላቀ ሚና እንዳለው ተናግረዉ ለዚህም ሁሉም አካላት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት
የዞኑ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ የፈጠራ ሥራዎችን በትምህርት ቤቶች በማጠናከር አምራች ኃይል እንዲፈጠር መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ተማሪዎች ለፈጠራ ሥራ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ራሳቸውን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት በማላቀቅ ከሀገር አልፎ በአለም ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል ።
የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ አስቻለው ስባኒ በበኩላቸው ከኮሌጁ ተመርቀው የሚወጡ ሙያተኞችን ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር ገበያ ተኮር ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ለማስቻል እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ከመንግስት በተጨማሪ የግል ባለሃብቶች በዘርፉ የበኩላቸዉን ሚና እንዲወጡ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አመላክተዋል ።
ወደ ቴክኒክ ሙያና ስልጠና ዘርፍ የሚቀላቀሉ ተማሪዎችን ደካማ አድርጎ ማሰብ ትክክል ባለመሆኑ ይህ እሳቤ እንዲለወጥ ግንዛቤ መፍጠር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
እስካሁን የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ለአብነት ያነሱት የኮሌጁ የቦርድ አባላት ወጣቱ ትውልድ ራሱን በሙያ አብቅቶ የተለያዩ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን የሚያከናውንበት ተቋም በመሆኑ ዜጎች በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል ።
#ዘገባው የወልቂጤ ኤፍ ኤም ሬድዮ ነው











