አገና ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ከሰኔ 20/2016 ጀምሮ የተለያዩ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገለፀ።
ሐምሌ 19/2016 አገና
ኮሌጃችን በ2016 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ሪፖርት ግምገማና የ2017 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ገምግሞ ወደ ተግባር ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ ልዩ የዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ በማዘጋጀትና በማኔጅመንት ደረጃ የአፈፃፀም አቅጣጫ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት ያህል፦
- የክረምት በጎ አድራጎት ስራዎች ዝርዝርና እና ተጠቃሚ ዜጎችን የመለየት ስራ ተሰርቶ ወደ ትግበራ የተገባ ሲሆን በዚህም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ አመካከትን በዜጎች ንቁ ተሳትፎ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መደበኛ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን በተለያዩ ዘርፎች እንደየዝንባሌያቸው ማሰልጠን፤ በአጫጭር ስልጠና ክህሎት ማስጨበጥና ለቀጣይ ሰልጣኞች ቅበላ ምቹ ሁኔታ የመፍጠርና ዓላማ ያለው ስልጠና ለ152 አካባቢ ተማሪዎች በአይሲቲ፤ በጋርመንት፤ በፈርኒቸር፤ በብረታ ብረት(ሜካኒክስ) እና በኤሌክትሮ ቴክኖሎጂ ስልጠና ዘርፎች የክህሎት ስልጠና በመሰልጠን ላይ ይገኛሉ
- የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ ለማሳካት 2500 የሚደርሱ የችግኝ ጉድጓዶች ተዘጋጅተው ለአቦካዶ፤ ለቡናና እና ሌሎች ኢኮኖሚካል ጥቅም ያላቸው ችግኞች የአጥር ዝግጅት በማጠናቀቅ የአቦካዶ፤ ሮዝምሪና የጉሎ ዛፍ ዘር የመትከል ስራ የተከናወነ ሲሆን ተግባሩ የሚቀጥል ይሆናል።
- በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በጋበር በጎ-አድራጎት ድርጅት ለሚገነባው የአገና ከተማ ላይበራሪ የዲዛይን ማሻሻል፤ የጥገና ዝርዝር ጥናት በማዘጋጀት እንዲሁም የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ነፃ አገልግሎት በመስጠት ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን የክትትልና ቁጥጥር ስራውን በተሰጠን የድርጅቱ ውክልና መሰረት የሙያ አገልግሎት በመስጠት ማህበረሰቡን የማገልግል ስራ እንዲሰራ ተደርጓል።
- ለቀጣይ የትግበራ ምዕራፍ ምቹ ለማድረግ አሰልጣኝ መ/ራን በመጠቀም የኢንተርፕራይዝ የስልጠና ፍላጎትና ክህሎት ክፍተት የመለየት፤ የቴክኖሎጂ ዳሰሳ ጥናት የማድረግ እንዲሁም የግብርና ባለሙያ በማካተት የእሴት ሰንሰለት ትንተና ጥናት የማድረግ ስራዎች የማነቃቂያ ስልጠና በመስጠት የስራ ምደባ የተሰጠ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት የኢንደስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ዘርፍ የክህሎት ክፍተት መሙላት የሙያስችል ሰነድ ዝግጅት በማጠናቀቅ ስልጠና የሚጀመር ይሆናል።
- የገቢ አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የምርት ክፍል ኢንተርፕራይዝ በሚካኒክስና በፈርኒቸር ስልጠና ክፍል አሰልጣኞችና ሰልጣኞች በጥምረት በማደራጀት ምርቶችን በማምረት የውስጥ ወጪ በመቀነስ እንዲሁም በሽያጭ የገቢ አማራጭ በሚሆንበት ደረጃ የማድረስ ስራ እየተሰራ ሲሆን የንብ ማነብ ስራ በስፋት ለመስራት ዘመናዊና ባህላዊ ቀፎዎችን በመጠቀም እየተሰራ ይገኛል።በሌላ በኩል በአውቶሞቲቭ ስልጠና ዘርፍ ስልጠና መስጠት ለመጀመር የሚስችል የባጃጅ ግዢና ሌሎች ተያያዥ የተሽከርካሪ ድጋፍ ከአገና ከተማና ከእዣ ወረዳ መንግስት በማግኘት ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅቱ ተጠናቋል የሮዝመሪ፤ የጉሎ ዛፍ፤ የፖም ችግኞችን ተከላ እና ስንዴ ለመዝራት የሚያስችል 1.5 ሄክታር መሬት በማረስ ዝግጁ ተደርጎ ወደ ትግበራ በመግባት የሮዝመሪ ችግኝ ተከላ የመጀመሪያ ዙር የተከናወነ ሲሆን ቀሪ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
- በግብርናው ዘርፍ በእንስሳት እና ሰብል ልማት ላይ ስልጠናዎች ለማስጀመር የሚያስችል ግዝያዊ ስልጠና ክፍሎች በኮሌጃችን አሰልጣኞች የተገነቡ ሲሆን በውስጥ ገቢ አቅም በጀት በመመደብ በአሰልጣኞቻችን እየተገነባ ያለው 300 ካሬ ላይ ያረፈውን የጋርመንት ስልጠና ክፍል ወርክሾፕ ማጠናቀቅ የሚያስችል ግብዓት በማሟላት ወደ ተግባር ተገብቷል።በሌላ በኩል በአልፋ-ቤት ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የተተከለው የሶላር ሃይል ከስልጠና መስጫነት ባሻገር ኮሌጁን ሙሉ ማስጠቀም የሚያስችል አቅም ለማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በአሁን ወቅት የኮሌጁ ምድረ-ጊቢ ለቀጣይ መደበኛ ሰልጣⶉችና ለክረምት የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ስልጠና ምቹና ማራኪ የማድረግ ስራዎች ተከናውነዋል፤በመከናወን ላይም ይገኛሉ።
በመጨረሻም ከሐምሌ 26/2016 ጀምሮ በተለየው የአሰልጣኞችና አስተዳደር ሰራተኞች ክህሎት ክፍተት መሰረት በተቋም ውስጥ አቅም ለሚፈቱ የክህሎትና የአመለካከት ክፍተቶችን ለመሙላት በተዘጋጁ 06 የስልጠና ሞጁሎችን በመጠቀም የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጥ ይሆናል ሲል የዘገበው የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ነው።
ለበለጠ መረጃ
ድህረገፃችን፡ www.agenacollege.edu.et እንዲሁም የቴሌግራም ቻናላችንንን https://t.me/agenacollege2007 ይቀላቀሉ!!
በፌስቡክ ገፃችን www.facebook.com/agenacollege2007 ይከታተሉን!!





